ዶክተር ሜሪ ኒል በእረጅም እና አድካሚ የትምህርት እና ልምምድ ጊዜ አሳልፋ በአጥንት ቀዶ አካሚነት ስራዋን የምትሰራ ሴት ነበረች::
ዶክተር ሜሪ በዚህ የትምህርት እና ተመራማሪነት ውስጥ በማለፏ በሞት የደርሶ መልስ ታሪኮች ላይ ተጠራጣሪ የነበረ አቋም ነበራት:: በእረፍት ጊዜዋ በደቡብ አሜሪካ ቺሊ በሚባል ሃገር በሚገኘው ወንዝ ውስጥ እየተንሳፈፈች ለመዝናናት ተዘጋጅታ ጉዞዋን ወደዚሁ ቦታ አቀናች:: ነገር ግን ትዝናናበት የነበረው አነስተኛ መንሳፈፊያ በድንጋይ ውስጥ በመያዙ ከ 2.5ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ ውስጥ ተይዛ ለ30 ደቂቃዎች ቆየች::
በቦታው የደረሱ የነፍስ አድን ባለሙያዎች ሰውነቷን ወንዙ ተፍቶት በወንዙ ዳር ስላገኙት የሚችሉትን ያህል ህክምና ካደረጉላት በኃላ ከከባድ የሰውነት አደጋ ጋር ተመልሳ በሕይወት ለመኖር በቅታለች:: በዚያች ሞትን በቀመሰችባቸው ደቂቃዎች የሆነችውን ትናገራለች::
እንደ ዊኪ ፒዲያ መረጃ ይህ የ’ሞት ደርሶ መልስ ተሞክሮ’ ጉዳይ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሲነገር የነበረ ቢሆንም እ.ኤ.አ ከ1890ቹ ጀምሮ በፍልስፍና እና በስነ-ልቦና ተመራማሪዎች ሲጠና የነበረ ጉዳይ ነው:: ነገር ግን በተለይ በ1960ቹ የተለየ ትኩረት ሲሰጠውና ሲጠና ቆይቷል:: በ2011 በወጣው የኒዎርክ ሳይንስ አካዳሚ አመታዊ ዘገባ በሰሜን አሜሪካ ግዛት ብቻ ወደ 9ሚሊዮን የሚደርሱ የሞት ደርሶ መልስ ባለታሪኮች መኖራቸውን አስታውቋል::
በሚሊዮን የሚቆጠሩ እነዚህ ባለታሪኮች ወይም ግለሰቦች ምንም እንኳን ከተለያየ የዓለም ክፍል ከተለያየ የሃይማኖትና ባህል እንዲሁም ከተለያየ የእድሜ ክልል የተወጣጡ ቢሆንም ተመሳሳይ የተሞክሮ ታሪክ እንዳላቸው ጥናቶች ይመሰክራሉ:: ይህም ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንዲሰጠውና እንዲጠና እድሉን ከፍ አድርጎታል::
እነዚህ የደርሶ-መልስ ታሪኮች በተመሳሳይ መልኩ በዋናነት:-
- እንደሞቱ ማወቅ/መገንዘብ
- ከምንም አይነት ህመም ነፃ መሆንና ደስተኛነት ከሰላም ጋር
- ከእራስ ሰውነት ወጥቶ እራስን የመመልከት ሁኔታ
- በጠባብ ክፍል መገኘት እና ወደላይ ወይም ወደታች በፍጥነት የመውጣት ወይም የመውረድ ስሜት
- የብርሃን ፍንጣቂ ማየት ወይም ወደምትያስደንቅ ብርሃን ውስጥ መግባት
- የብርሃን ፍጥረታት ወይም ደግሞ ቀድሞ የሞቱ የቤተሰብ አባላትንወይም ጏደኞችን የመገናኘ ዕድል ማግኘት
- የህይወትንሙሉ ቆይታ እንደፊልም መመልከት
- ወደፊት ለመሄድ ወይም ወደኃላ ለመመለስ ትእዛዝ መቀበል/በመካከልም ለመሻገር ወይም ወደፊት ለመሄድ መታለፍ ያለበት ክልል ወይም አጥር እንዳለ ማወቅ
- ወድ ስጋ ዳግመኛ ተመልሶ የመግባት ወይም የመምጣት ሁኔታዎችን ያካተቱ ናቸው::
ዶክተር ሜሪ ኒል ስለሆነው ነገር እንደዚህ ትናገራለች:: “ከውሃው ውስጥ በህይወት እንደማልወጣ ስለተረዳሁ እና ትንፋሼንም መቆጣጠር እንደማልችል ሳውቅ በቃ ይሄው ነው ብዬ አስቤ በቃ አምላክ ሆይ ፈቃድህ ይሁን ብዬ ፀለይኩ::
በእግዚአብሄር መኖር የማምን ሰው ብሆንም ይንን ያህል እግዚአብሄር በህይወቴ አስፈላጊ አይደለም ብዬ ማስብ ሰው ነበርኩ:: ነገር ግን በነዚያ ቅፅበት ሰከንዶች ውስጥ ከልቤ እና ከእውነት በቃ የሆነው ሆኗል ግን አንተ ሁሉን ተቆጣጠረው ብዬ በእግዚአብሄር ላይ ሁሉንም ተውኩት:: በጣም እንደምሰቃይ እና ሁሉም እንደሚያበቃ ነበር እየጠበኩ የነበርኩት:: ነገር ግን የሚገርም ሰላም እና እረፍት ይሰማኝ ጀመረ:: በእግዚአብሄር እጅ እንደተያዝኩ ገብቶኝ ነበር:: ልክ የአንድ አዲስ ህፃን ትናንሽ ጣቶች ሰው ሲይዝ በአንድ ጊዜ በንፁህ ደስታ ተስፋ እና ፍቅር እንደሚወረስ እንደዚያ እየተሰማኝ ነበር እራሴን ያገኘሁት:: ነገር ግን እኔ ነበርኩ አዲሱ ህፃን:: ጠንቅቆ እንደሚያውቀኝ እንደሚወደኝ እና እንደተቀበለኝም አውቄ ነበር” ::
መንፈሷ ከስጋ ሰውነቷ በቅፅበት ሲለይ እና ከወደላይ ሆና ወንዙን እና ጏደኞቿን ትመለከት እንደነበረ እንዲሁም ጏደኞቿ እና የነብስ አድን ባለሙያዎቹ ዳግመኛ መተንፈስ እንድትችል ሲያደርጉት የነበሩትን ሙከራ ሁሉ በ አየር ላይ ከስጋዋ ውጪ በመሆን ተንሳፍፋ ትመለከት እንደነበረ ትናገራለች::
“በመቀጠልም ብርሃንን የለበሱ ሰዎች ከበቡኝ ደግሞም ይዘውኝ በሃይል ወደላይ ወጡ::የወሰዱኝ ቦታ ምድር ላይ በሌሉ ውብ ቀለማት ይተዋበ ቦታ ነበር:: በምድር ላይ የኖርኩትን ኑሮ ከህፃንነቴ ጀምሮ ያሳለፍኩት ደግም ሆነ ክፉ እንደ ፊልም ሆኖ ይታይ ነበር::ነገር ግን እንደእኔ ብቻ ሳይሆን በነዚያ ሁሉ የህይወቴ ጊዜያት በህይወቴ ውስጥ ተካተው የነበሩ ሰዎች ሁሉ ስሜት እንደራሴ ሆኖ ይሰማኝ ነበረ እና በጣም አሁን ላይ ያለኝ ህይወት እንዲለወጥ ምክንያት ሆኖኛል::” “ምንም እንኳን እዛው መቆየት ብፈልግም ‘አሁን ጊዜሽ አይደለም በምድር የምትሰሪው ስራ አለ’ በማለት በዚያ ውብ እና በፍቅር የተገነባ ቦታ እንዳልቆይ ከለከሉኝ:: ቀጥሎ በጣም በህመም ውስጥ ሆኜ በስጋ አካሌ ውስጥ እራሴን አገኘሁት::”
ምንም እንኳን ትልቅ ቁጥር ያለው የሞት ተሞክሮ ታሪክ ከዓለም ዙርያ ቢመጣም ሳይንስ እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ እና ተቀባይነት ያለው ተሞክሮ ነው ለማለት እልደፈረም:: ነገር ግን ይህ ተሞክሮ ከሰላሳ አመታት በላይ በተደረጉ በተለያዩ ጥናቶች ድምዳሜ መሰረት ማንንም ሊያሳምን የሚችል እውነታ እንዳለው መረዳት ይቻላል:: መቼም ይህ የሰው ህይወት እንዲሁ ከሞት በኃላ መሄጃው ማይታወቅበት ጠፍቶ ከንቱ ሆኖ ይቀራል ብሎ ማመን የፈጣሪን አርቆ አሳቢነት እና ጠንቃቃነት እንደመጠራጠር ሆኖ ቢቆጠር አያስደንቅም:: ምክንያቱም የሰው ልጅ እንኳን ብዙ ነገሮችን በብዙ ጥበብ ሲሰራ ብዙ እቅዶችን በውስጡ ይዞ ይሰራል:: ብዙ ታሪኮች አሉ:: በሚቀጥለው የፅሁፍ ልጥፍ ማንበብ ይችላሉ::
Jeffrey Long, MD with Paul Perry “Evidence of the after life”(200-202)
https://www.womansworld.com/posts/comfort/near-death-experience-mary-neal#