ሳይንቲስቶች የአንድን አለት ወይም ቅሪተ-አካል ዕድሜ ሲናገሩ ብዙ ሰዎች በማጉያ መሳርያ ከላያቸው ላይ የሚያነቡት ነገር እንዳለ አድርገው ያስባሉ። ነገር ግን እንዲህ አይደለም። በአጭሩ ሳይንቲስቶች የአለቶችን ወይም ቅሪተ አካላትን ዕድሜ ለማወቅ ራዲዮ አክቲቭ የሚባሉ ኢለመንቶችን ባህርይ ይጠቀማሉ። ይህም ራዲዮ ሜትሪክ ዴቲንግ ቴክኒክ በመባል ይታወቃል።
አሁን ባለው የዴቲንግ ቴክኒክ አሰላል መሰረት ለምሳሌ አንድ ኪ.ግ የሚመዝን ከዩራኒየም አይሶቶፕ (ዩራኒየም-238) ኢለመንት ብቻ የተሰራ አለት ግማሹ ኪሎው ወደ ሊድ አይሶቶፕ ኢለመንት ለመበስበስ ቢያንስ 4.5 ቢሊየን አመታት ይወስድበታል። ስለዚህ ይህ አለት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሊድነት ከተቀየረ 9 ቢሊየን አመቱ ነው እንላለን።(ዩራኒየም ወላጅ ኢለመንት ሲባል ሊድ ደግሞ ዶውተር ኢለመንት ይባላል)
ነገር ግን ትልቁ ችግር ይህ የዕድሜ ማስያ መንገድ በውስጡ ሊረጋገጡ የማይችሉ ግምቶችን(Assumptions) አካቶ ስሌትን የሚሰራ በመሆኑ ነው።
ከእነዚህ ግምቶች ወስጥ:-
- በመጀመርያ ይህ አለት ሙሉ ለሙሉ ከወላጅ ኢለመንት ብቻ የተሰራ ነው ብሎ የመገመት (ሳይንቲስቶች ይህ አለት ሲፈጠር ዶውተር ኢለመንት አብሮ አልንበረም ብለው በመነሳት ይጀምራሉ)
- አለቱ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በውጫዊ ተጽዕኖ አማካኝነት ተጨማሪ የወላጅ ኢለመንት አይነት አለቱ ላይ አልተጨመረበትም ብሎ አስቦ የመነሳት
- አለቱ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በውጫዊ ተጽዕኖ አማካኝነት ተጨማሪ የዶውተር ኢለመንት አይነት አለቱ ላይ አልተጨመረበትም ብሎ አስቦ የመነሳት
- አለቱ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የወላጅ ኢለመንት ከላዩ ላይ በውጫዊ ተጽዕኖ አልተቀነሰበትም ብሎ የማሰብ
- አለቱ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የዶውተር ኢለመንት ከላዩ ላይ በውጫዊ ተጽዕኖ አልተቀነሰበትም ብሎ የማሰብ
- የወላጅ ኢለመንት የመበስበስ ፍጥነቱ(decay rate) ከመጀመርያ አንስቶ እስካሁን ሳይቀየር እንዳሁኑ ነው ብሎ የማሰብ እነዚህ ሁሉ ሊረጋገጡ የማይችሉ እና ግምት ብቻ የሚወሰድባቸው ነገሮች ናቸው። ይህም ስሌቱን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀያየር አቅም አለው። (ውጫዊ ተጽእኖች የምንላቸው ለምሳሌ እንደ አልትራ ቫዮሌት ጨረር፣ውሃ፣አየር ፣ሌሎች ራዲዮ አክቲቭ ኢለመንት የሚለቁት ቅንጣጢቶች …. )
ፖታሲየም አርገን የሚባለው ዴቲንግ ቴክኒክ ከሌሎቹ የዴቲንግ ቴክኒክ መንገዶች የተሻለ ነው ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ከላይ የጠቀስኳቸውን ግምቶች ሳይንቲስቶች አስበው ስለሚነሱ ተመሳሳይ ችግር አለበት።
ለምሳሌ ያህል ዕድሜያቸው የሚታወቁ አለቶች በፖታሲየም አርጎን ዴቲንግ ቴክኒክ ዕድሚያቸው ሲሰላ ከትክክለኛው ዕድሜያቸው አንጻር ያለውን ልዩነት እንመልከት። (በእሳተ ገሞራ አማካኝነት የተፈጠሩ አለቶች ስለሆኑ እና እሳተ ገሞራው የፈነዳበት ጊዜ ስለሚታወቅ የአለቶቹ ትክክለኛ እድሜ ይታወቃል።) –
- ሁዋላላይ ባዛልት ቦታ ሃዋይ የፈነዳው በ1800-1801 የተሰላው እድሜ 1.32-1.76 ሚሊየን ዓመት(ትክክለኛ ዕድሜ 220 ዓመት!)
- ኤትና ባሳልት (ተራራ) ቦታ ሲሲሊ የፈነዳው በ1972 የተሰላው ዕድሜ ከ 210,000 -490,000 ዕድሜ (ትክክለኛ ዕድሜ – 48 ዓመት!)
- ጋውሩሆ (ተራራ) ቦታ ኒው ዚላንድ የፈነዳው በ1954 የተሰላው ዕድሜ ~ 3.5 ሚሊየን ዓመት (ትክክለኛ ዕድሜ 66 ዓመት!)
- ኪላዌ ኢኪ ባዛልት ቦት ሃዋይ የፈነዳው በ1959 የተሰላው ዕድሜ ~ 1.7 ሚሊየን አመት (ትክክለኛ ዕድሜ 60 ዓመት!)
- ሄለን (ተራራ) ቦታ ዋሺንግተን የፈነዳው በ1986 የተሰላው እድሜ 2.8 ሚሊየን አመት (ትክክለኛ ዕድሜ 34 ዓመት!) – ሌሎችም ብዙ ….
እንግዲህ ይህ ስሌት በውስጡ በያዛቸው ግምቶች የተነሳ ጥቂት አስርት አመታት ያስቆጠሩ አለቶችን እንዲህ አይነት ውጤት ከሰጠ በዕርግጥም ሺህ አመታት ያስቆጠሩ አለቶችን ምን ያህል የተሳሳተ ውጤት ሊሰጥ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ግልጽ ነው እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ይህ ስህተት የመጣው ከሳይንስ ሳይሆን ሳይንቲስቶቹ ከወሰዱት ግምት ነው።
ከጠቀመዎት ለሌላ ሰው ያጋሩ።
(ምንጭ :- Andrew Snelling, “Excess Argon: The ‘Achilles’ Heel’ of Potassium-Argon and Argon-Argon Dating of Volcanic Rocks,” Impact, January 1999, Andrew Snelling, “Conflicting ‘Ages’ of Tertiary Basalt and Contained Fossilized Wood, Crinum, Central Queensland Australia,” Technical Journal 14, no. 2 (2005): p. 99–122.)